ብሄራዊ የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ኃይል የጀመረውን ፀረ- ኮንትሮባንድ ኦፕሬሽን አጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸ።

ብሄራዊ የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ኃይል የጀመረውን ፀረ- ኮንትሮባንድ ኦፕሬሽን አጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸ። ========================= አዲስ አበባ 29/06/2016 ዓ.ም (የንቀትሚ) ብሄራዊ የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ኃይል በሱማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ ዙሪያና በሲቲ ዞን ወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ለመቆጣጠር እያካሄደ ያለውን ፀረ- ኮንትሮባንድ ኦኘሬሽን አጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸ። ብሄራዊ የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ኃይል በምስራቁ ሀገራችን ክፍል የሚስተዋለውን ከፍተኛ የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ዝውውርን ለመቆጣጠር ወደ ኦፕሬሽን መግባቱንና በርካታ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዙንና የጀመረውን ኦፕሬሽን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል። በዚሁ መሠረት ግብረ-ኃይሉ በአምስት ቀናት ብቻ ባካሄደው ጠንካራ ኦኘሬሽን ከኮንትሮባንዲስቶቹ ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ እያደረገ በርካታ የኮንትሮባንድ እቃዎችን የያዘ ሲሆን ከተያዙት ውስጥ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ የተለያዩ ሞባይሎች እና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እንዲሁም የተለያዩ ጨርቃ ጨርቅ ቦንዳዎችና ምንጣፎች እንደሚገኙበት ግበረ- ኃይሉ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አስታውቋል። ግብረ-ኃይሉ የያዛቸውን የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በጅግጅጋ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን መጋዘን ገቢ ተደርገዋል ብሏል መግለጫው። እስከአሁን በተካሄደው ኦፕሬሽን እና ለተገኘው ውጤት የህዝቡ ተሳትፎ በጣም ከፍተኛ ነበር ያለው የግብረ-ኃይሉ መግለጫ በቀጣይም ተጠናክሮ ለሚቀጥለው የፀረ-ኮንትሮባንድ ኦፕሬሽን ውስጥ ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

Share this Post