ኢትዮጵያ በቀጣይ ሶስት አመታት ውስጥ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚያስችላትን ዝግጅት እያደረገች ነው::
===================
አዲስ አበባ 16/04/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) ኢትዮጵያ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ለ20 ዓመታት በታዛቢነት የተሳተፈችበትን የአለም ንግድ ድርጅት በአባልነት ለመቀላቀል ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ፡።
ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በአለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድር ሂደት ለ 4 ጊዜ በታዘቢነት በመሳተፍ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም እስካሁን አባል አለመሆኗን ያነሱት ሚኒስትሩ አሁን ላይ የድርድር ሂደቱ በከፍተኛ ትኩረት እየተመራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እ.ኢአ እስከ 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ ድርድሩን በማጠናቀቅ አባል ለመሆን የእቃዎችና የአገልግሎት ንግድ ኦፈር፣የገቢ ንግድ ፈቃድ አሰራር መረጃዎች፣ የመንግስት የንግድ ድርጅቶች መረጃ፣ ንግድና ንግድ ነክ ህጎች መረሀ ግብር እንዲሁም የወጪ ንግድ ድጎማና የግብርና ምርቶች ድጋፍ ሰነዶችን የማሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በአራተኛው ዙር ድርድር ከአባል ሀገራት 181 ጥያቄዎችን የተቀበለች ሲሆን የድርድር ጥያቄዎቹ ማጠንጠኛ የሆነውና በአሁኑ ወቅት በአማካኝ 14 በመቶ የሆነውን የታክስ መጠን በ5ኛው ዙር ድርድር አሻሽሎ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አቶ ገብረመስቀል አስረድተዋል፡፡
በአዲስ መልክ የተዋቀረውና የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድርን እና ቀጣናዊ የንግድ ትስስሮችን የሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ በዛሬው እለት ውይይት አካሂዷል፡፡