በአፍሪካ በትምህርት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ለምርታማ ትውልድ ግንባታ ወሳኝ ነው፦ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን

በአፍሪካ በትምህርት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ለምርታማ ትውልድ ግንባታ ወሳኝ ነው፦ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ================= አዲስ አበባ 07/05/2016(ንቀትሚ) በአፍሪካ በትምህርት ዘርፍ ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ለምርታማ ትውልድ ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳለው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ገለጹ። ሊቀ መንበሩ የአፍሪካ ሕብረት 47ኛው የቋሚ ተወካዮች መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የዘንድሮው 47ኛው የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ገባኤ '21ኛው ክፍለ ዘመንን የዋጀ ትምህርት በአፍሪካ' በሚል መሪ ሀሳብ በትምህርት ዘርፍ ላይ በማተኮር ከአንድ ወር በኋላ ይካሄዳል። የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት እንዳሉት በአፍሪካ የተከሰቱ ግጭቶች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ለዚህ ስኬት የሀገራት አንድነትና ትብብር ወሳኝ ነው። እንደ ኢዜአ ዘገባ የአባል ሀገራት ተወካይ አምባሳደሮችን ያቀፈው የሕብረቱ ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ የሕብረቱ ስብሰባ ይዘቶችን በማርቀቅ ብሎም የጋራ መግባባት እንዲደረስ ቁልፍ ሚና ያለው አካል መሆኑን ገልጸዋል። ኮሚቴው በስብሰባው መልከ ብዙ አህጉራዊ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮችን በትኩረት እንዲያጤንና ከአጀንዳ 2063 የተጣጣመ ውይይት እንዲኖረው አሳስበዋል። ኮሚቴው በአፍሪካ ሰላም፣ ልማትና ትስስርን ዕውን ለማድረግ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ምክክር በማድረግ በሁነኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ የውሳኔ ሀሳቦችን እንዲያቀርብም ነው አቅጣጫ ያስቀመጡት። የዘንድሮው የአፍርካ ህብረት ጉባኤ መሪ ቃል በትምህርት ላይ ማተኮሩ አምራች ኃይል ለመፍጠርና ምቹ አህጉር ለመገንባት ትምህርት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ትልቅ ትርጉም ስላለው እንደሆነ ገልፀዋል።

Share this Post