ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ስትራቴጅካዊ የሆነ እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ማህበራዊ ግንኙት አላት፡፡ ሀገራት በኢኮኖሚው መስክ የሚኖራቸው ግንኙነትና ትብብር የሚሳለጥበት ዋንኛ መንግድ ንግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ዘመናትን የተሻገር፣ የህዝብ ለህዝብ መስተጋብርና ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ የንግድ ግንኙነትም ጥናትን መሰረት ያደረጉ ድርድሮች እና ስምምነቶች እየተካሄዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፌደራል አስፈጻሚ መ/ቤቶችን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2021 መሰረት የውጭ ንግድ ግንኙቶችን የመመስረት፣ የንግድ ስምምነቶችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መደራደርና መፈራረም፣ የተፈረሙ ስምምነቶችን የማስተግበር ስልጠን አለው፡፡ በዚህም መሰረት መ/ቤታቸን በተለያዩ ዓለም አቀፍ፣ ቀጣናዊ እና ሁለትዮሽ ንግድ ድርድሮችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ሀገራችን እስካሁን 20 የሁለትዮሽ ንግድ ስምምነቶች፣ ሦስት የጠረፍ ንግድ ስምምነቶች እና በርካታ የንግድ ትብብር መግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርማለች፡፡ ከተፈረሙት የሁለትዮሽ ንግድ ስምምነቶች መካከል ሦስቱ ልዩ የንግድ ስምምነቶች ሲሆኑ ሌሎቹ የንግድ ትብብር ስምምነቶች ናቸው፡፡ ሀገራችን የተፈራረመቻቸው 3ቱም ልዩ የንግድ ስምምነቶች የተፈረሙት ከጎረቤት ሀገራት (ሱዳን፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን) ጋር ሲሆን እነኝህ ስምምነቶች ቀረጥን ጨምሮ ንግድን ለማስፋፋትና ለማሳደግ የሚያግዙ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ በሀገራችን እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ከአጠቃላይ ንግዳችን 19 በመቶ ያህል ድርሻ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ጎረቤት ሀገራት ከፍተኛውን የንግድ ድርሻ ይይዛሉ፡፡ እ.ኤ.አ ከ2018-2022 ባሉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ለሀገራችን ወጪ ንግድ በአፍሪካ ከፍተኛ መዳረሻ ከሆኑት ሀገራት መካከል ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ሱዳን እና ኬንያ ከ1ኛ-4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ 2018-2022 ዓ.ም ባሉት ያለፉት አምስት አመታት ከጎረቤት አገራት ማለትም ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የነበራት አጠቃላይ አመታዊ አማካይ የንግድ ልውውጥ መጠን 483.39 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ከዚህ ጠቅላላ የንግድ ልውውጥ ሶማሊያ 303,764,403 ዶላር (63%) ደርሻ በመያዝ ቀዳሚ የንግድ አጋር ነች፡፡ በተመሳሳይ ጅቡቲ በ108,105,023 ዶላር (22.3%)፣ ሱዳን በ40,294,221 ዶላር (8.3%)፣ ኬንያ በ25,007,100 ዶላር (5.2 በመቶ) ድርሻ በመያዝ ተከታዩን ደረጃ ሲይዙ ደቡብ ሱዳን ደግሞ በ6,218,344 ዶላር የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች፡፡ ሀገራችን ወደጎረቤት ሀገራት ከላከቻቸው ወጪ ምርቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት፣ ቡና፣ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬ፣ ቁም እንሰሳት እና የእጽዋት ስራስር ውጤቶች ናቸው፡፡ ከጎረቤት ሀገራት በስፋት የምናስገባቸው ምርቶች ደግሞ የምግብ ዘይት፣ ቤንዚን፣ ቀይ ሽንኩርት፣ የጽህፈት መሳሪዎች፣ ማሽላ፣ ማሽኖች፣ የወተት ዱቄትና ሌሎች ፕሮቲን የበዛባቸው ምግቦች ናቸው፡፡ የጠረፍ ንግድ ሀገራት በጋራ ከሚያካሂዷቸው የንግድ ትብብር አይነቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የጠረፍ ንግድ ዓላማው ሸቀጦችን ስምምነቱን በሚያደርጉት ሀገራት ማዕከላዊ ክፍል በቀላሉ ማግኘት ለማይችሉ ጠረፍ አካባቢዎች ላይ ለሚኖሩ ህዝቦች መሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚያገኙበትን የገበያ ስርዓት ማመቻቸት ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ከሱድን፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከጂቡቲ ጋር የጠረፍ ንግድ ስምምነት አላት፡፡ እነዚህ የጠረፍ ንግድ ስምምነቶች በድንበር አካባቢ ያሉ ህገወጥ እና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቀነስ (መደበኛ ያልሆኑ የንግድ ልውውጦችን መደበኛ ለማድረግ)፣ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ መጠን ለመጨመር፣ በድንበር አካባቢዎች ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ናቸው። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የጠረፍ ንግድን ለማቀላጠፍ እና ለማሻሻል ከኬንያ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ውይይቶችን እያካሄደች ትገኛለች፡፡ ድርድርና ስምምነቶቹ የሀገራችንን እና የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ባስጠበቀ መልኩ ጊዜ ተወስዶባቸው በጥንቃቄ የሚካሄዱ ናቸው፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ምርቶችን አይነት እና መጠን በማብዛት የመዳረሻ ገበያዎችንም የማስፋት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ የተደረጉ ሁለትዮሽ የንግድ ስምምነቶችም ይሀንኑ ዓላማ በማገዝ ሀገራዊ የወጪ ንግድ ግኝትን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ያላት እምቅ ሀብት እና ባለልዩ ጣእም ምርቶች በተቀባይ ሀገራት ዘንድ ምርቶቿ ተመራጭነት አላቸው፡፡ ስለሆነም እነዚህን ምርቶቻችንን ከምርት እስከ መጨረሻው ግብይት ሂደት ድረስ ተፈላጊውን የጥራት ደረጃ ጠብቆ ለውጪ ገበያ በማቅረብ እድሉን ወደ ፍሬ ቀይሮ መቋደስ ያስፈልጋል፡፡

Share this Post