የንግድ ፍቃድ እድሳት ለ10 ቀናት ተራዘመ፡፡

የንግድ ፍቃድ እድሳት ለ10 ቀናት ተራዘመ፡፡ ==================== አዲስ አበባ 1/05/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) የንግድ ፍቃድ እድሳት ቀናት ለቀጣይ 10 ቀናት መራዘሙን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሲስተም መቆራረጥን መነሻ በማድረግ ለሚቀጥሉት አስር ቀናት የንግድ ስራ ፍቃድ እድሳት ያለ ቅጣት አገልግሎቱ እንዲሰጥ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ የሲስተም መቋረጥ ለተወሰኑ ቀናትና በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ የነበረ ቢሆንም ከዞንና ከወረዳ ርቀው የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብን የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ግንዛቤ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም በቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሪፈረንደም መለያየትን ተከትሎ አዳዲስ ክልሎች ለሳምንታት አገልግሎት ያልሰጡበትን ቀን ታሳቢ በማድረግ መራዘሙን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅና ደንብ በሚደነግገው መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ለአስር ቀናት ብቻ ያለ ቅጣት እንዲስተናገዱ መወሰኑን ያስታወቀው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን እድል በመጠቀም በተሰጡት ቀናት የንግድ ፍቃዳቸውን እንዲያድሱ አሳስቧል፡፡ ከሀምሌ 1/2015ዓ.ም እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 1.4 ሚሊዮን አገልግሎቶች በኦንላይን መሰጠቱን ተጠቁሟል፡፡

Share this Post