የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች የበጀት ዓመቱን 6 ወራት እቅድ አፈፃጸም ገመገሙ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች የበጀት ዓመቱን 6 ወራት እቅድ አፈፃጸም ገመገሙ፡፡ ==================== አዲስ አበባ 08/05/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት በሀገር ውስጥ ንግድ፣ በወጪ ንግድ እና በጥራት መሰረተ ልማት በተሰሩ ስራዎች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናግረዋል፡፡ ህገ-ወጥ ንግድን እና በፋብሪካና በድርጅቶች ላይ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥነቶችን በመከታተል ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የገለጹት ሚኒስትሩ ለቀሪ ስድስት ወራት እቅድ ስኬት ሁሉም የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ አንድነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የሀገራችን ንግድ በተቋም የሚመራበት ስርዓት ከተጀመረ መቶ አመታትን ያስቆጠረ እንደመሆኑ ያሉበትን በርካታ ችግሮች በመፍታት ወቅቱ የሚጠይቀውን የንግድ ዘርፍ ለመፍጠር በንግድ ስርዓት ዲጂታላይዜሽን፣በህግ-ማእቀፍ ማሻሻያ፣ የሰው ሀይል በማሟላት እና በቢሮ ግንባታ ትልቅ ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጥራት መሰረተ ልማትና ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ናቸው፡፡ የንግድ አገልግሎቶችን ዲጂታል ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች በርካታ ውጤቶች መታየታቸውንና የህግ ማእቀፎች እንዲሻሻሉ መደረጉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የሚመጥን የቢሮ እድሳቶችን እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በግምገማ መድረኩ የተገኙ ሰራተኞችም በውስጥ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በእቅድ ትግበራ ሂደቱ የተስተዋሉ ችግሮችን እና በቀጣይ ቢስተካከሉ ያሏቸውን ሀሳብ አንስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

Share this Post