ባለፉት 6 ወራት 189,698 ተሽከርካሪዎች የቴሌ ብር መተግበሪያን ለመጠቀም ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ 15/6/2015(ንቀትሚ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዘርፉን የግማሽ በጀት ዓመት እቅድ አፈፃጸም ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል፡፡ በግምገማ መድረኩ ላይ ባለፉት 6 ወራት በርካታ ስኬቶች መከናወናቸውን ከቀረበው ሪፖርት ላይ መረዳት ተችሏል፡፡

እንደ ስኬት ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ የታለመለት የነዳጅ የድጎማ ስርዓት ተግባራዊነትን ከመከታተል አንጻር የተከናወኑ ተግባራት በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሹ ጉዳይ ነው፡፡

መንግስት በነዳጅ ምርት ላይ ያካሄደውን ሪፎርም ተከትሎ የዚህ ምርት የግብይት ሂደት በጥሩ ዲሲፒሊን እንዲመራ የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም አስፈላጊነት አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህም በመንግስት በኩል ታምኖበት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከኢትዮቴሌኮም ጋር የቴሌ ብር መተግበሪያ ስልትን መጠቀም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

ከዚህ ስምምነት ማግስትም የቴሌ ብር መተግብሪያ በመላ ሃገሪቱ እንዲተገበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ውይይት ይሄው ቴክኖሎጂ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ስርዓቱ በጥሩ ዲሲፒሊን እንዲመራ በርከታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የተደረገው ጥረትም ፍርያማ ሆኖ ባለፉት 6 ወራት በመላ ሃገሪቱ 189,698 ተሽከርካሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን መመዝገባቸውን ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡ በዚህም መሠረት በኦሮሚያ 81,574፣ በአማራ 49,667፣ በአዲስ አበባ 16,560፣ በደቡብ 15,340፣ በድሬደዋ 8,226፣ በሲዳማ 6,148፣ በሃረሪ 2,898፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትጵያ 2,359፣ በሶማሊ ክልል 3,281፣ በአፋር ክልለ 1,468፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ 1,338 በጋምቤላ 839 የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች በዚህ ስርዓት ለመገልገል ምዝገባ አካሂደዋል፡፡

ከተሽከርካሪዎች ምዝገባ በተጓዳኝ የትግራይ ክልልን ሳይጨምር ካሉት 1,106 ማዳያዎች መካከል 1,060 የሚሆኑት ማደያዎች በዚህ ስርዓት ለመገልገል የተመዘገቡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 972 የሚሆኑት ትራንዛክሽን መጀመራቸው ተረጋግጧል፡፡

የዚህ ስርዓት ተግባራዊ መደረግ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ፍጹም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ እንደ ምቹ መደላድል ከሚጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ከላይ እንደተመላከተው ይህ የቴክኖሎጂ አማራጭ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን ስርዓት ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር አንዳንድ ክልሎች የተሻለ አፈጻጸም ቢኖራቸውም በተቃራኒው ዝቅ ያለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ክልሎች መኖራቸውም በቀረበው ሪፖርት ተገጿል ፡፡ ይህ መልካም ጅማሮ እነዳለ ሆኖ በቀጣይ 6 ወራት በትኩረት መሰራት የሚገባቸው በርካታ የቤት ስራዎች እንዳሉም ግንዛቤ መያዙ ተገቢ ነው፡፡

በሃገራችን እንደ ስትራቴጂካዊ ከሚቆጠሩት ምርቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የነዳጅ ምርት በጥሩ ዲሲፒሊን እንዲመራ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተጨማሪ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሚና የጎላ በመሆኑ እነዚህ አካላትም ሚናቸውን በአግባቡ በመወጣት ለሪፎርሙ ስኬት የራሳቸውን አበርክቶ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

 

 

Share this Post