ይዘት “ድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን” ለምን እና እንዴት?
ተስፋዬ ታደሰ
የንግድ ምዝገባ እና የንግድ ስራ ፈቃደ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ፍትሃዊ፣ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ በማድረግ የንግዱ ማህበረሰብ እና መላው ህብረተሰብ ከንግድ ስርዓቱ የሚጠብቀውን አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ እርካታን ማሳደግ እና በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የንግድ ምዝገባ እና የንግድ ስራ ፈቃድ አሰጣጥን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በማድረግ የንግድ ስርዓቱ ለመረጃ አያያዝ አመቺ እንዲሆን፣ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመግታት የሚያስችል፣ ለመንግስት፣ ለህዝብ እና ለሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን የንግድ ዘርፍ መረጃ እንዲያገኙ ማስቻልም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የንግድ ስርዓቱን ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና መልካም አስተዳደር የሰፈነበት እንዲሆን እና የአገሪቱን ራዕይ ለማሳካት እንዲቻል ዘመናዊ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ሥርዓት እንዲኖራት ለማድረግ ታልሞ ወደ ተግባር ከተገባ ሰነባብቷል፡፡
እነዚህን ጉዳዮች እውን ለማድረግ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008፣ ደንብ ቁጥር 461/2012 እና የኢትዮጰያ የንግድ ህግ 1243/2013 በኢፌደሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቀው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን የህግ ማእቀፎች በማስተግበር ደረጃ ትልቁን ኃላፊነት የተሰጠው ደግሞ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው፡፡ የህግ ማእቀፎቹን በሚገባ ስራ ላይ በማዋል የሚፈለገው ሀገራዊ እና ማህበረሰባዊ ፋይዳ እንዲመጣ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሚሰጡ አገልግሎቶች ውስጥ የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ስራ አንዱ ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዓላማም የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ስራ እንዴት እና ምን ዓላማን ለማሳካት እንደሚሰራ ለማስገንዘብ ነው፡፡
ድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ማለት የንግድ ስራ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ ፈቃዱን የወሰደው አካል በተሰጠው የንግድ ፈቃድ መሰረት እየሰራ መሆኑን በአካል ሄዶ ክትትል የሚደረግበት ሂደት ነው፡፡ ድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ነጋዴዎች በአወጡት የንግድ ስራ ፈቃድ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያውን ተከትለው እየሰሩ መሆኑን የማረጋገጥ እና ክትትል የማድረግ ስራ ነው፡፡ ዓላማውም ያለንግድ ፈቃድ የሚሰሩ፣ በወቅቱ ያላሳደሱ፣ ከአወጡት ፈቃድ ዘርፍ ውጪ የሚሰሩ በጥቅሉ አዋጁ ከሚፈቅደው ውጪ የሚነግዱትን ተከታትሎ በመለየትና ቴክኒካዊ ድጋፍ በማድረግ የእርምት እርምጃ ወስዶ ህጋዊውን የአሰራር ስርዓት ብቻ ተከትለው እንዲሰሩ ማስቻል ነው፡፡
ድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን የሚከናወነው በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008፣ ደንብ ቁጥር 461/2012 እና መመሪያ ቁጥር 935/2015ን መሰረት አድርጎ ሲሆን የኢንስፔክሽን ስራውን እንዲሰራ ኃላፊነት የተሰጠውም የኢፌዴሪ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በተዋረድ ያሉ የንግድ ቢሮዎች እና ጽ/ቤቶች ናቸው፡፡
የእነዚህ መስሪያ ቤቶች የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክን ባለሙያዎች ለኢንስፔክሽን ስራ ወደ ንግድ ተቋማት ሲወጡ ነጋዴዎች በትክክለኛው መንገድ እየሰሩ መሆኑንና አለመሆኑን የሚያረጋግጡት በዚህ ጽሁፍ ከላይ የተገለጹትን አዋጅ፣ ድንብና መመሪያ መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በሚደረገው የማረጋገጥ ስራም ህጉን ጠብቀው የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ ከህግ ውጪ የሚሰሩ ነጋዴዎችም ይገኛሉ፡፡
በግኝቱ መነሻነት ህጉን ተላልፈው ሲሰሩ የተገኙት ነጋዴዎችን/የንግድ ድርጅቶችን/ ዜጎችንም ሀገርንም ወደሚጠቅመው ወደ ህጋዊው አሰራር ለማስገባት ሦስት አይነት እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ የመጀመሪያው እርምጃ ኢንስፔክሽን በተሰራበት ሠዓት በኢንስፔክሽን ባለሙያዎች ወዲያውኑ የሚሰጥ የማስተካከያ ምክረ ሀሳብ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ቀላልና ነጋዴው ስራውን ሳያቆም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያስተካክለው የሚችለው ጥፋት/ግድፈት/ ሲሆን ነው፡፡
ሁለተኛው እርምጃ አስተዳደራዊ እርምጃ ነው፡፡ አስተዳደራዊ እርምጃ ማለት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወይም የኢንስፔክሽን ስራውን በአከናወነው የንግድ ቢሮ ወይም ጽ/ቤት የሚወሰድ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ የንግድ ድርጅት እሸጋ፣ የንግድ ምዝገባ ወይም ፈቃድ እገዳ፣ ስረዛ ወይም መሰል እርምጃዎችን የሚያካትት ነው፡፡ ለአስተዳደራዊ ቅጣት ከሚዳርጉ ጥፋቶች ውስጥም የንግድ ፈቃድን በወቅቱ አለማሳደስ፣ ከንግድ ስራ ፈቃድ ዘርፍ ውጪ መስራት፣ አድረሻ አለማሳወቅ፣ ባስመዘገበው የንግድ ፈቃድ አድራሻ ሳይገኝ ሲቀር፣ሐሰተኛ መረጃን በመጠቀም ንግድ ፈቃድ ማውጣት/ማደስ…የሚሉት ይገኙበታል፡፡
እነዚህ እና ሌሎችም ጥፋቶችን በፈጸመ ነጋዴ ወይም የንግድ ድርጅት ላይ ሊወሰዱ የሚችሉት እርምጃዎች በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 ላይ በግልጽ ተደንግገዋል፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ያክል የንግድ ስራ ፈቃድ ማደስ የሚገባው በየበጀት ዓመቱ ከሐምሌ 1 እስከ ታህሳስ 30 ነው፡፡ በዚህ የ6 ወር ጊዜ ገደብ ውስጥ የንግድ ፈቃዱን ያላሳደሰ ነጋዴ ከጥር 1 እስከ ሰኔ 30 ቀን ባለው ጊዜ በጥር ወር ሁለት ሽ አምስት መቶ ብር እና ለሚቀጥለው እያንዳንዱ ወር አንድ ሽ አምስት መቶ ብር ቅጣት ከፍሎ ያሳድሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያልታደሰ የንግድ ፈቃድ ይሰረዛል፡፡
ሦስተኛው የእርምጃ አይነት ሕጋዊ እርምጃ ነው፡፡ ሕጋዊ እርምጃ ሕግን ለመተርጎም ስልጣን በተሰጣቸው የፍትህ ተቋማት የሚወሰድ ሲሆን ነጋዴዎችን ለዚህ የሚዳርጉ የጥፋት አይነቶችም በርከት ያሉ ናቸው፡፡ በሐሰተኛ የንግድ ምዝገባ ወይም የንግድ ፈቃድ መስራት፣ በአልታደሰ የንግድ ፈቃድ ሲሰራ የተገኘ፣ ሐሰተኛ መረጃን በማቅረብ የንግድ መዝገብ( የንግድ ስም፣ የንግድ ፈቃድ) ያወጣ፣ የንግድ ስራ ፈቃድን ለ3ኛ ወገን እንዲጠቀምበት አሳልፎ መስጠት፣ የንግድ ስራ አድራሻ ለውጥ በወቅቱ አለማሳወቅ ሕጋዊ እርምጃ ሊያስከትሉ ከሚችሉ ጠፋቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
እነዚህን እና ሌሎችም በዚህ ጽሁፍ ያልተጠቀሱትን ሕጋዊ እርምጃ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጥፋቶችን በፈጸሙ አካላት ላይ የሚወሰዱት እርምጃዎች የገንዘብ ቅጣት እና የእስራት ብይኖች ናቸው፡፡ በገንዘብም ሆነ በእስራት የሚፈረደው የቅጣት ውሳኔ ደረጃ እንደየጥፋቱ አይነት የሚለያይ ቢሆንም በገንዘብ ከ አምስት ሺ እስከ ሦስት መቶ ሺ ብር በእስራት ደግሞ ከ3 ወር ቀላል እስራት እስከ 15 ዓመት የሚደስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ 980/2008 በዝርዝር ያስረዳል፡፡
ስለዚህ መላው የንግድ ማህበረሰባችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆንም ሆነ ከተጠያቂነት ለመዳን እነዚህን የንግድ ማሳለጫ አዋጅ፣ ድንብና መመሪያ በሚገባ ተረድቶ በእውቀት እና ህጋዊ መሰረቱን ተከትለው መስራት ይገባቸዋል እንላለን፡፡