የጥራት መሰረተ ልማት ዘርፍን አገልግሎት አሰጣጥንና ተደራሽነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት ይሰራል፡፡
=======================
አዲስ አበባ03/10/2016ዓ.ም (ንቀትሚ) በ2017 በጀት ዓመት የጥራት መሰረተ ልማት ዘርፍን ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከተደራሽነትና በጥራት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ አንፃር ትራንስፎርም ማድረግ እንደሚገባ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የጥራት መሰረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮነን አስታወቁ፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የጥራት መሰረተ ልማት ዘርፍና ተጠሪ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር በመሆን የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ የተወያዩ ሲሆን ዘርፉን ከአገልግሎት አሰጣትና ከተደራሽነት አንፃር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ላይ በትኩረት እንደሚሰራና እንደ ዘርፍ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሳደግ ወረቀት አልባ አገልግሎት መስጠት፣ ጥራት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ከተደራሽነት አንፃር ከሀገር አልፈን በጎረቤት አገር ቅርንጫፍ በመክፈት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ አቶ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
የጥራት መሰረተ ልማት ዘርፍን ትራንስፎርም ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው እኒዚህ ምቹ ሁኔታዎች ከአሰራር ስርዓት አኳያ አራት ደንቦች የፀደቁና 2 ረቂቅ አዋጆች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ተዘጋጅተው ለሚመለከተው ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑ፣ የጥራት ፖሊሲን ለማፀደቅ የመጨረሻ ምእራፍ ላይ መድረሱ እንዲሁም የጥራት መሰረተ ልማት ህንፃ ግንባታ እየተጠናቀቁ መሆኑና አቅርቦት ተሟልቶ ወደ ስራ ስለሚገባ እቅዱን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡