ኢትዮጵያ በ11 ወራት የወጪ ንግድ 9.81 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት አዲስ ታሪካዊ ሪከርድ አስመዘገበች

ኢትዮጵያ በ11 ወራት የወጪ ንግድ 9.81 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት አዲስ ታሪካዊ ሪከርድ አስመዘገበች

(አዲስ አበባ፡ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም) በ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከተያዘው ግብ በላይ እጅግ አበረታችና ታሪካዊ ውጤት በማስመዝገብ በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ገለጹ።

ክቡር ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ውስጥ 8.48 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፣ ከ9.81 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በማስመዝገብ የተቀመጠውን ዕቅድ 115.66 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

ይህ አስደሳች አፈጻጸም ባለፈው የ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው የ7.21 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር፣ የ36.10 በመቶ ወይም የ2.6 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው ከፍተኛ ዕድገት ያሳየ ነው።

ሚኒስትሩ አያይዘውም በዚህ ታሪካዊ ስኬት ብቻ ሳንገደብ፣ በቀሪው የበጀት ዓመቱ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ፣ ከተቀመጠው ዓመታዊ ዕቅድ በላይ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ይህ ታሪካዊ ውጤት እውን እንዲሆን ሌት ተቀን ለሰሩና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አምራቾች፣ ላኪዎች እና ለመላው ባለድርሻ አካላት የተሰማቸውን ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። በጋራ ጥረታችን የኢትዮጵያን ዘላቂ ብልጽግና እናረጋግጣለን ብለዋል።

Share this Post