የፋብሪካዎች ኢንስፔክሽን ሥራን በተመለከተ ከክልሎች ጋር ምክክር ተደረገ

የፋብሪካዎች ኢንስፔክሽን ሥራን በተመለከተ ከክልሎች ጋር ምክክር ተደረገ (አዲስ አበባ ፡ ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም) በጥራት መሠረተ ልማትና ማረጋገጥ ዘርፍ ሥር የሚሠሩ የፋብሪካዎች ኢንስፔክሽን ሥራዎችን በክልል ደረጃ ንግድን ለማስተዳደር ሥልጣን ላላቸው አካላት በውክልና ለመስጠት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ ለውይይት ቀረቧል። ይህ የዳሰሳ ጥናት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራት ማረጋገጫ መሪ ሥራ አስፈጻሚ በአቶ አንዱዓለም ክንዴ የቀረበ ሲሆን፣ በምክክር መድረኩ ላይ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች የንግድ ቢሮዎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። በቀረበው የምክክር ሰነድ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ እንዳለው መኮንን ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሚኒስትር ዲኤታው አቶ እንዳለው በሰጡት ማብራሪያ፤ ጠንካራ የገበያና የፋብሪካ ኢንስፔክሽን ሥራዎችን መሥራት የዜጎችን ጤና ለማረጋገጥና ጤናማ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻል ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። ይህንን ጠንካራ የኢንስፔክሽን ሥራ እስከ ቀበሌ ድረስ ለማውረድም፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሥራውን ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች በውክልና ሰጥቶ ማሰራቱ ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች አንጻር ሲታይ እጅግ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥራውን በውክልና ከመስጠት ባለፈ በሥልጠናና በአቅም ግንባታ ረገድ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ የገለጹት ሚኒስትር ዲኤታው፣ የዕለቱ መድረክም የዚሁ አቅም የማሳደግ ጥረት አካል መሆኑን ጠቁመዋል። የገበያ ኢንስፔክሽን ሥራ ሙሉ በሙሉ የክልሎች ኃላፊነት ሲሆን የፋብሪካ ኢንስፔክሽን ሥራ ግን በውክልና የተሰጠ መሆኑ በመድረኩ ተመላክቷል።

Share this Post