የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ስርዓትን በጠንካራ የህግ ማዕቀፍና ተቋማዊ ድጋፍ ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው ተባለ
(አዲስ አበባ ፡ ሰኔ 16፣ 2018 ዓ.ም ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ስርዓት (Warehouse Receipt System) ህጋዊ ማዕቀፎች፣ ጥቅሞችና የአሰራር ዘዴዎች ላይ ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀመረ።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድ ትስስርና የወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ታዜር ገ/እግዚአብሔር እንደገለጹት፤ የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ስርዓትን በጠንካራ የህግ ማዕቀፎችና የቁጥጥር ስርዓት በመተግበር ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው። ስርዓቱ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከአዋጁ በመነሳት ደንብ ተዘጋጅቶ መጽደቁንና ዝርዝር መመሪያዎችም በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።
የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ስርዓትን በጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት ለመተግበር ሁሉም ተዋናይ አካላት የተወከሉበት ቦርድ ተቋቁሟል። ይህም በተዋናዮች መካከል መተማመንን በመፍጠር ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል አቶ ታዜር።
ይህ ሥርዓት አርሶ አደሮች፣ የህብረት ሥራ ማህበራት እና ነጋዴዎች ምርታቸውን ደረጃቸውን በጠበቁና በተፈቀዱ መጋዘኖች ውስጥ በማከማቸት የባለቤትነት ደረሰኝ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ይህንን ደረሰኝ በባንኮችና በፋይናንስ ተቋማት ዘንድ እንደ መያዣ (Collateral) በመጠቀም ብድር ማግኘት የሚቻልበት አሰራር መዘርጋቱም ተገልጿል።
ይህም አርሶ አደሮች ምርታቸውን በምርት ወቅት በዝቅተኛ ዋጋ በአስቸኳይ ከመሸጥ ይልቅ በመጋዘን አስቀምጠው፣ የተሻለ የገበያ ዋጋ እስኪያገኙ ድረስ እንዲጠብቁ በማድረግ ገቢያቸውን የማሳደግ ሰፊ እድል ይፈጥርላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የመጋዘን ደረሰኝ ሥርዓት ፦
• ከምርት በኋላ የሚደርሰውን ብክነት (Post-harvest loss) ለመቀነስ፣
• የምርት ጥራትን ለማሻሻል፣ እና
• በገበያው ላይ ግልጽነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሳሪያ መሆኑ ተጠቁሟል።
በአጠቃላይ የሥርዓቱ ተግባራዊነት የአርሶ አደሮችን ገቢ ከማሳደጉም ባሻገር፣ የግብርናው ዘርፍ የሚፈልገውን መዋቅራዊ ለውጥ ለማፋጠንና የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማጠናከር አጋዥ እንደሚሆን ተመልክቷል።
በዚህ የማስገንዘቢያ መድረክ ላይ ከባንኮች፣ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ከግብርና ምርት አቀናባሪዎች፣ ከህብረት ስራ ዩኒየኖችና ከአምራቾች የተውጣጡ በርካታ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።